የኬንያ ባለስልጣናት ስለኩልብዮው ጥቃት መዋሸታቸውን አዲስ ትንታኔ ጠቆመ

ከሶማልያዋ ኩልቢዮው የተገኙ የቪዲዮ ምስሎችን እና ሌሎችንም ማስረጃዎች በየግላቸው ያጠኑ ሁለት የደህንነት ተንታኞች፣ በዚህ ዓመት ቀደም ሲል የአል-ሸባብ ታጣቂዎች የኬንያ የመከላከያ ኃይል የጦር ሠፈር ጥሰው ገብተው፣ በርካቶችን ከገደሉ በኋላ ከአካባቢው መሸሻቸውን እንደሚያምኑ ገለጹ፡፡

ይህም የጦር ሠፈሩ ቅጥረ-ክልል አልተደፈረም ሲሉ ከሚሟገቱትና ዘጠኝ ወታደሮችን ብቻ እንዳጡ ከሚናገሩት የኬንያ ባለስልጣናት አስተያየት ጋር ይጋጫል፡፡

የሶማሊያ ታጣቂዎች ኩልብዮው የሚገኘውን የኬንያ የጦር ሠፈር ያጠቁት እ.ኤ.አ. ጥር 27 ቀን ሲሆን፣ ከተሸከርካሪ ላይ ቢያንስ ሁለት ቦምቦችም ጣብያው ላይ ከወረወሩ በኋላ በርከት ያሉ ሰዎች የተሳተፉበት የመሬት ላይ ጥቃት አድርሰዋል፡፡ የጥቃቱ ውጤት በተመለከተ የሚሰነዘሩ ቁጥሮች ግን የተለያዩ ናቸው፡፡

የአል-ሸባብ የፕሮፓጋንዳ ክንፍ አል-ካቲያብ ወዲያውኑ ታጣቂዎች የጦር ሠረፉን በቁጥጥር ይዘውት እንዲሁም በርካታ የኬንያ ሰለባዎችን የሚያሳዩ ምስሎችን ለቅቋል፡፡ በምላሹም የኬንያ ጦር፣ የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር እንዲሁም የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ማስተባበያ ማቅረባቸውን ቀጥለው የአል-ሸባብ ምስሎች ከሌላ ቦታ የመጡ እንደሆኑና ከኩልቢዮው የተገኙ እውነተና የቪዲዮ ምስሎች እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡

የኬንያ የጦር ሠራዊት ከኬንያዊ ኤንቲቪ የቴሌቭዥን ጣብያ የቪዲዮ ባለሞዎችን ጋብዞ ከጥቃቱ ከአስር ቀናት በኋላ የኩልቢዮውን የጦር ሠፈር እንዲጎበኙ አድርጓል፤ ጥር 27 ቀን ጠ የኬንያ መከላከለያ ኃይል የኩልቢዮ የጦር ሠፈርን ይቆጣጠር እንደነበር ያሳያል የተባለ በድሮን የተቀረጸ ምስልንም ለቅቋል፡፡

“በየትኛውን ቅጽበት ጣብያችን አልተወረረም፡፡ የኬንያ የመከላከያ ኃይል ያንን ጣብያ እንደተቆጣጠረ ይገኛል… በየትኛውም መልኩ ቅጥረ-ክልሉ አልተጣሰም”  ብለዋል የቤተ መንግስቱ አፈ ቀላጤ ማኖአህ ኢሲፒሱ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኬንያ መገናኛ ብዙሃን መተረማመስ ያላጣውም ቢሆን ስኬታማ ግን የሆነ የጦር ሠፈሩን የመከላከል እርምጃን በዝርዝር ዘግበዋል፡፡

ስለዚህ እውነታው የት ነው ያለው? ኬንያ ኩልቢዮ ላይ ወታደራዊ እንቅፋት ገጥሟት ነበር? ወይንስ የተቃጣባት ጥቃት ላይ ተገቢውን ምላሽ ሰጥታ ችግር ውስጥ በወደቀው የጠላት ኃይል ላይ ከባድ ጉዳትን አድርሳለች? የጦር ሠፈራውን ከሚጠብቁት ወደ 120 የሚጠጉ የኬንያ ወታደሮች መካከል ለመትረፍ በቅተዋል? ምን ያህሎቹስ ለአገራቸው ሕይወታቸውን ገብረዋል?

ከእነዚህ ጥያቄዎች በዛ የሚሉቱ ገና ወደፊት የሚመለሱ ይሆናሉ- ነገር ግን የጦር ሠፈራው ቢያንስ በከፊል ተጥሶ እንደነበር ይበልጡኑ ግልጽ እየሆነ ይገኛል ይላሉ ለሕዝብ ይፋ በሆነው መረጃ ላይ ጥናት ያደረጉ ሁለት ምዕራባውያን የትንታኔ ባለሞያዎች፡፡

የሦስተኛ ዲግሪ እጩ የሆኑትና ለአፍሪካን ዲፌንስ ሪቪው የሚጽፉት ኮንዌይ ዋዲግንተን የኤንቲቪ ቪዲዮ እና የአልሸባብ የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮ ኩልቢዮው ውስጥ ያሉትን ተመሳሳይ ሕንጻዎች እና አካባቢያዊ ገጽ   ታዎች እንደሚያሳዩ ጠቁመው፣ ይህም ሁለቱም ቪዲዮዎች በተመሳሳይ ሥፍራ ነገር ግን በተለያየ ጊዜ እንደተቀረጹ ያሳያሉ ይላሉ፡፡ ከዚህ በመሳነትም በሚከተለው ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፡-“የኬንያ የመከላከያ ኃይል እንደሚለው የአል-ሸባብን ጥቃት መክቶ አልመለሰም፡፡ ቅጥረ-ክልሉ በእርግጥም ተጥሶ ነበር- ጥሰቱ ደግሞ የአል-ሸባብ ታጣቂዎች የሠፈራ ጣብያውን ለመዝረፍ እስኪችሉ ድረስ ነበር፡፡”

ዋዲንግተን ምክንያታቸውን ሲያቀርቡ እንዲህ ይላሉ፡- “አል-ካታይብ የለቀቀው ምስል በመጣስ ላይ ያለ ወይንም የተጣሰ የጦር ሠፈርን የሚያሳይ ይመስላል… ጣብያው ሙሉ በሙሉ ባይጣስም እንኳ፣ በሚቃጠሉ ተሸከርካሪዎች እና ወታደራዊ ከለላዎእ ላይ የተሰቀሉ ሰንደቅ ዓላማዎችን እንዲሁም የጦር መሣርያዎችን እና ጥይቶችን ይዘው ወዲያ ወዲህ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን የሚያሳዩ ምስሎች ቢያንስ የጦር ሠፈሩ ቅጥረ-ክልል እንደተጣሰ፣ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ያህልም የመከላከያ ኃይሉ ጸጥ እንደተሰኘ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ ያም በኬንያ የመከላከያ ኃይል ከቀረበውና ጥቃቱ ሙሉ በሙሉ ድባቅ ተመትቷል ከሚለው ዋነኛ ትርክት ጋር የሚጣረስ ነው፡፡”

ነገር ግን የኬንያ ወታደሮች በኋላ ላይ ወደሠፈራ ጣብያው ተመልሰው ዳግመኛ እንደያዙት እንደሚያምኑ ገልጸዋል፤ ይህም በመልሶ ማጥቃት ወይንም የሶማሊያ ታጣቂዎቹ ስላፈገፈጉ ሊሆን ይችላል፡፡ “አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች፣ ስማቸው ያልተገለጸ የኬንያ የመከላከያ ኃይል አባልን በመጥቀስ፣ ከመከላከያ ኃይሉ የተወሰነው ክፍል አፈግፍጎ እንደነበር እናም በኋላ ሳይመለስ እንዳልቀረ ዘግበዋል፡፡ እንዲህ ያለው ክስተት እስካሁን ካለው ማስረጃ ጋር የሚስማማ ነው” ሲሉ ጽፈዋል፡፡

ሌላኛው ተንታኝ ጄኮብ ቢደርስ አል-ሸባብ የለቀቃቸው በርካታ ፎቶዎች በኬንያ መንግስት የድሮን ምስሎች ላይ ከሚታዩት ሥፍራዎች ጋር የሚስማሙ ናቸው ይላሉ፡፡

“ይህም በተከላካዮቹ ተመክቶ ከመመለስ ይልቅ አል-ሸባብ የጦር ሠፈሩን ቅጥረ-ክልል በመጣስ ከውስጥ በነጻነት መንቀሳቀስ መቻሉን የሚያሳይ ነው፡፡ አል-ሸባብ በጦር ሠፈሩ በጠቅላላ በተለያዩ ሥፍራዎች ላይ ፎቶዎችን ማንሳት ችሏል….. በአንድ የጦር ሠፈሩ አካባቢ ብቻ ሳይሆን” ሲል በኪንግስ ኮሌጅ ለንደን የጦርነት ጥናቶች የትምህርት ክፍል ምሩቅ የሆኑት ቢደርስ ጽፈዋል፡፡

እንዲህ ሲሉም አክለዋል፡- “የፎቶዎቹ ስብስብ ደርዘኖችን ያህል የኬንያ የመከላከያ ኃይል ወታደሮችን አስከሬኖች እንደማሳየቱ፣ ዘጠኝ ወታደሮች ብቻ ናቸው የሞቱት የሚለውን የመንግስት አስተያየት ይጣረሳል፡፡” ሁለቱም ተንታኞች የሶማሊያ ታጣቂዎች ለምን ያህል ጊዜ የጦር ሠፈሩን ተቆጣጥረውት እንደቆዩ ለመናገር አልቻሉም፡፡ ሆኖም ቢደርስ ከድሮን ምስሎቹ በመነሳት አልሸባብ በርካታ ወታደራዊ ተሸከርካሪዎችን ሰርቆ እንደሸሸ ይገምታሉ፡፡

earth-image-1
Kulbiyow is located in southern Somalia near the Kenyan border

የኩልቢዮው ጥቃት ፋይዳ ባለፈው ዓመት በኤል-አዴ ከደረሰው ጥቃት ጋር በመመሳሰሉ ነው፡፡ በቀዳሚው ጥቃት የኬንያ የመከላከያ ኃይል በተመሳሳይ ሁኔታ ከመቶ በላይ ወታደሮችን አጥቷል፡፡ ሁለቱ ክስተቶች ተጠያቂነትን የሚሸሽን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ባሕልን እንዲሁም ያለፉትን ስህተቶች አንስቶ ለመወያየት እና ለመማር ቸልተኛ መሆንን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡

ከኤል-አዴ ዓብይ ትምህርቶች መካከል አንደኛው የኬንያ መከላከያ ኃይል/አሚሶም የጦር ሠፈሮች ከተሽከርካሪ በሚወረወሩ ቦምቦች በቀላሉ እንዳይጣሱ ተጨማሪ ወታደራዊ ምህንድስና እንደሚያስፈልግ ነው፡፡

የኩልቢዮው የጦር ሠፈር ከኤል-አዴ ጋር በመጠኑ እጅጉን የሚመሳሰል ነው- ሁለቱም በአንድ መቶ አለቃ ወይንም ከመቶ አለቃ በጥቂቱ ከፍ የሚሉ ወታደሮችን ይዘዋል፡፡ ይህም ከኤል-አዴው ጥቃት በኋላ አሚሶም ሩቅ ቦታዎች ላይ መቶ አለቃን የመሳሰሉ ጥቂት አባላት ያላቸው ወታደራዊ ክፍሎችን ማስቀመጡ ለአደጋ አጋላጭ በመሆኑ እንዲተው አስተያየቶች ከመሰጣተቸው በተቃራኒ ነው፡፡

ቢደርስ ሁለቱን ጥቃቶች ተከትሎ የሃቆቹን የሕዝብ ግንኙነት ጉዳዮች ለመያዝ የተደረገበት ሙከራ ያመሳስላቸዋል ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡ የኬንያ መንግስት የአል-ሸባብ ጥቃትን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን መደበቅን መቀጠሉ፣ አልሸባብ የክስተቶችን ትርክት እንዲቆጣጠር አስችሎታል፡፡

“በኤል-አዴው ጊዜ እንዳጋጠመው ሁሉ ስለኩልቢዮው ጥቃት አብዛኛው መረጃ የመጣው ስማቸው ካልተገለጸ በሥፍራው የነበሩ ሰዎች መረጃዎች እና ከአል-ሸባብ ፕረፓጋንዳ ነው፡”

“ከዚህም በተጨማሪ ለወደፊቱ በኬንያ ወታደሮች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ሊቀንስ የሚችል የተጠያቂነት ጥረትን ያፍናል” ሲሉ ይሟገታሉ ቢደርስ፡፡ “የተገደሉትን በርካታ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች ብዛት በይፋ ለመቀበል ወይንም በዓብይ ፍልሚያዎች ያጋጣሙ ቴክኒካዊ እንከኖችን ለመቀበል አሻፈረኝ ማለቱ፣ ለምርመራ እና ለተጠያቂነት ፈቃደኝነት እንደሌለው ያሳያል፡፡”

የቢደርስ እና ዋዲንግተን ትንታኔ በአንዳንድ የኬንያ የብዙሃን መገናኛ ዘገባዎች የተደገፈ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ወታደር ለኬንያው ዴይሊ ኔሽን እንዲህ ብሏል፤ “ከሦስተኛው ቪባይድ (ከተሸከርካሪ ላይ የሚወረወር ቤት የተሠራ ፈንጅ መሣርያ) ሲፈነዳ፣ መከላከያችን ተስፋ ቢስ እንዲሆን ተደረገ፡፡ የአል-ሸባብ ታጣቂዎች በየሥፍራው እየተሯሯረጡ ነበር፡፡ ነብሴ አውጭኝ ስንል መሮጥ ጀመርን፡፡”

በሥፍራው የነበሩት የኬንያ መከላከያ ኃይል ኮማንደር ሌላ ታሪክ ይናገራሉ፡፡ በጥቃቱ የቆሰሉት ሻለቃ ዴኒስ ጂረንጌ ለዴይሊ ኔሽን “እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ በጣብያው ነበር፡፡ በታጣቂዎች ተጥሶ ቢሆን ኖሮ አሁን አላናግራችሁም ነበር፡፡ ሞቼ የሆነ ቦታ ላይ እሆን ነበር፡፡ እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ጣብያውን ተከላክለናል፡፡ አልሸባብ ነው የሸሸው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኬንያ እና የወዳጅ አገራት ባለስልጣናት የኬንያ የመከላከያ ኃይል ኩልቢዮው ላይ ላሳየው ጀግንነት ሙገሳቸውን ያቀረባሉ፡፡ የብሪታንያው የውጨ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የኬንያ መከላከያን “ቆራጥ ምላሽ” ያደነቁ ሲሆን፣ መከላከያው “ ለጥቃቱ ምላሽ በመስጠት ምሳሌ የሚሆን የጀግንነት ደረጃን አሳይተዋል” ብለዋል፡፡

በኩልቢዮው ክስተት እ.ኤ.ኤ. ከ2011 የተጀመረው ኬንያ በሶማሊያ ባላትን ሰላም ማስከበር ያጋጠመው የቅርብ ጊዜው ክስተት ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (አሚሶም) አባል እንደመሆናቸው፣ የኬንያ ኃይሎች የ“ምድብ 2” ኃላፊነት አለባቸው፤ ይህም ደቡባዊውን የታችኛው እና የመካከለኛውን ጁባ አካባቢ የሚያካትት ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ መንፈስ ለማነቃቃት እና መከላከያውን ለመገምገም ሶማሊያ ውስጥ ያለውን የኬንያ ጦር ገብተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዚዳንቱ የሶማሊያን መንግስት ለማጠናከር ፖለቲካዊ ጥረቶችን እያደረጉ ይገኛሉ፤ ይህ ጥረታቸውም የሶማሊያ አቻቸውን ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ፋርማጆን በዚህ ሳምንት ማግኘትን ይጨምራል፡፡