ግብጽ የኢትዮጵያን ጎረቤቶች ማቅረቧን ቀጥላለች፤ የኤርትራ ባለስልጣናት ለጉብኝት ወደካይሮ አቅንተዋል

የኤርትራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ስለሁለትዮሽ ጉዳዮች ለመነጋገር የግብጽ መዲና ካይሮን ጎብኝቷል፡፡ ጉብኝቱ ግብጽ በአባይ ተፋሰስ እና በአፍሪካ ቀንድ አገራት ከምታከናውነው ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፡፡

የኤርትራው የልዑካን ቡድን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኦስማን ሳለህ እና በፕሬዚዳንቱ አማካሪ በየማነ ገብረአብ የተመራ ነው፡፡ ልዑካኑ ከአስመራ ወደግብጽ ጉብኝት ለማድረግ የተነሱት የግብጽ የልዑካን ቡድን አባላት የራሳቸው የአስመራ የሥራ ጉብኝት ካጠናቀቁ ከአንድ ሳምንት ብቻ በኋላ ነው፡፡

የኤርትራ የውጭ የመረጃ ሚኒስትር እንደሚለው ከሆነ የሁለትዮሽ ውይይቶቹ በሁለቱ አገራት መካከል አስቀድመውም የነበሩትን ምጣኔ ኃብታዊና የንግድ ግንኙነቶች ማጠናከር ላይ ያተኮሩ ሲሆን፣ እነዚህ ግንኙነቶችም የባሕር ኃብትን፣ ግብርናን፣ ታዳሽ ኃይልን፣ ጤናን፣ የባንክ እና የፋይናንስ አገልግሎቶችን የሚመለከቱ ናቸው፡፡

ሁለቱ አገራት ሕገ ወጥ የባሕር ላይ ውንብድናን በመከላከል ረገድ በጋራ ለመስራትም ተስማምተዋል፡፡ “ስምምነቱ ሽብርተኝነትን፣ የባሕር ላይ ውንብድናን እና ሕገ ወጥ የሰው ዝውውርን ለመግታት የትብብር እና የጥምረት ሥራ ማከናወንን ያካትታል” ብሏል የኤርትራው ሚኒስትር መስሪያ ቤት በድረ ገጹ ባቀረበው ዘገባ፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የኤርትራው የልዑካን ቡድን በግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሳሜህ ሾክሪ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን፣ የንግዱ ዘርፍ አባላት ጋርም ተገናኝቷል፤ የግብጽን የዓሣ እና የውሃ ውስጥ ልማት ፕሮጄክቶችን የጎበኘ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የግብጽ ምርቶች በሚቀርቡበት የካይሮ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ላይ ተሳትፎ ሌሎች በርካታ ተቋማትንም ጎብኝቷል፡፡

ሁለቱ ሚኒስትሮች ሐሙስ እ.ኤ.አ መጋቢት 23 ቀን ጉብኝቱን የተመለከተ ጠቅለል ያለ ውይይት አድርገው የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያላቸውን የጋራ ፍላጎት አረጋግጠዋል ይላል የመረጃ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ዘገባ፡፡

የግብጽ የመገናኛ ብዙሃን በኤርትራ ልዑካን የተደረገውን ጉብኝት ያረጋገጡ ሲሆን፣ ሁለቱ ወገኖች በአፍሪካ ቀንድ፣ በሶማሊያና በደቡባዊ የቀይ ባሕር ክልል ያሉትን እንቅስቃሴዎች በተመለከተ ውይይት አድርገዋል ከማለት የዘለለ ያቀረቡት ዝርዝር ጉዳይ ጥቂት ብቻ ነው፡፡

ኤርትራ የጎረቤቷ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ጠላት ስትሆን፣ ጉብኝቱ የአዲስ አበባ ባለስልጣናትን ደስ የሚያሰኝ አይሆንም፡፡ ከዚህ ቀደም ግብጽ፣ ኢትዮጵያ በጥቁር አባይ ወንዝ ላይ ስለምትሠራው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ስጋት እንደገባት የገለጸች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ ካይሮ ፕሮጄክቱን ለማስፈጸም የሚፈለገው የገንዘብ አቅም እንዳይገኝ ዓለም አቀፍ ለጋሾች እና አበዳሪዎች ላይ ጫና አሳድራለች ስትል ቅሬታዋን ታቀርባለች፡፡

ከዚህ ቀደም ከግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት የተሰጠ መግለጫ የግድብ ፕሮጄክቱ “ግብጽ ላይ ከፍተኛ ቁሳዊ፣ አካባቢያዊ እና ማኅበረ-ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳት ያደርሳል” ብሏል፡፡ ለዚህም ግብጻውያኑ የአካባቢያዊ እና ሥነ ውሃዊ የተጽዕኖ ግምገማ ጥናት ያለመካሄዱን እንደምክንያት ያቀርባሉ፡፡

ግብጽ ግድቡ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ላለው የሕዝብ ቁጥሯ የአባይን የውሃ ፍስሰት መጠን በከፍተኛ ደረጃ እንደማይቀንሰው ማረጋገጫ ትሻለች፡፡ ኢትዮጵያና ግብጽ ሱዳንን ጨምረው እ.ኤ.አ. ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን በዚህም መሠረት የፈረንሳዮቹ ቢ.አር.ኤል. እና አርተሊያ ኩባንያዎች የግድቡን ተጽዕኖ ግምገማ ጥናት ያከናውናሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የግብጹ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ ከሌሎች የአባይ ተፋሰስ አገራት ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረዋል፤ በታህሳስ ወር የዩጋንዳውን ዩዌሪ ሙሴቪኒ የጎበኙ ሲሆን በጥር ደግሞ የደቡብ ሱዳኑን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርን አስተናግደዋል፡፡

በሲሲ የታህሳስ ጉብኝት ወቅት ሙሴቪኒ የአባይን ኃብት ፍትሐዊ በሆነ መልኩ በመከፋፈል ዙርያ የሚመክር ጉባዔ እንደሚያስተናግዱ ያሳወቁ ሲሆን፣ ይህ ጉባዔ ግን እስካሁን ድረስ አልተከናወነም፡፡