የሳልቫ ኪር “ብሔራዊ ምክክር” ዓላማው ስልጣንን ማጠናከር ነው- የሟቹ ጆን ጋራንግ ባለቤት 

ሪቤካ ንያንዴንግ (በስተግራ) ከዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር ሲገናኙ፣ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 5 ቀን 2017 (ምንጭ የዩጋንዳ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት)

የሟቹ የሱዳን ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ኤስፒኤልኤም) መሥራችና መሪ ጆን ጋራንግ ደ ማቢዮር ባለቤት ሪቤካ ንያንዴንግ በደቡብ ሱዳን በቅርቡ ይፋ የተደረገው ‘ብሔራዊ ምክክር’ የጀርባ መግፍኤው ሰላማዊ እና አካታች ውይይትን ለመኮትኮት ሳይሆን በአገሪቱ ላይ የሳልቫ ኪርን ስልጣን ለማጠናከር ነው አሉ፡፡

ንያንዴንግ የሴኤልፒኤም ጂ10 እየተባሉ የሚጠሩ እውቅ የቀድሞ የፖለቲካ እስረኞችን ልዑካን ቡድን እየመሩ በአገሪቱ ያለውን ግጭት ለማስቆም ድጋፍ ይሰጡ ዘንድ ለመጠየቅ ወደዩጋንዳው መሪ ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቪኒ ባለፈው ሳምንት እንዳመሩ ተናግረዋል፡፡

“የፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒን ጥያቄ በመቀበል አንዳንድ የኤስፒኤልም መሪዎች እና እኔ ወደዩጋንዳ አቅንተናል፡፡ ግጭቱ እንዴት መቆም እንደሚችል ከእኔ እና ከኤስፒኤልኤም መሪዎች አስተያየት መስማት ፈልገው ነበር፡፡ ውይይታችን ፍሬያማ ነበር፡፡ ግጭቱ እንዴት መቆም እንዳለበት እንዲሁም ጦርነቱን ማቆም ከምንም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ስለመሆኑ ተነጋግረናል፤ እናም የሕዝባችን ሰቆቃ ይቆም ዘንድ የአገሪቱን ሰላም ለመመለስ መላ ለማግኘት በጥምረት መስራት እንዳለብን ሁላችንም ተስማምተናል” ብለዋል ንየንዴንግ፡፡

ከዘ ሜሴንጀር ጋር ባደረጉት ቆይታ የቀድሞዋ ሚኒስትርና የፕሬዚዳቱ አማካሪ ሰላምን ወደአገሪቱ ለመመለስ የሚያስችለው ብቸኛው መንገድ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ስልጣንን ላይ ሙጭጭ ማለታቸውን ትተው ወንበራቸውን እንዲለቁ የማሳመኛ መንገዶችን መፈተሽ ነው ብለዋል፡፡ “አገሪቷ እየተበታተነች ነው፡፡ ሕዝብ በየዕለቱ እየሞተ ነው፤ ሚሊዮኖች ወደጎረቤት አገራት አቋርጠው እየተሰደዱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ከየቀያቸው ተፈናቅለው በሰፈራ ጣብያዎች በመጥፎ ሁኔታ እየኖሩ ነው፤ እናም ጦርነቱ እየቀጠለ ነው” ብለዋል ንያንዴንግ፡፡

የስመ ጥሩ የኤስፒኤልኤም መሪ መበለት ለጥቀው የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርን አዲስ ብሔራዊ ምክክር “የፖለቲካ ፕሮጄክት” ሲሉ የሰየሙት ሲሆን አክለውም ከዚህ ይልቅ ደቡብ ሱዳን የሚያስፈልጋት አካታች ውይይት እንጅ በመንግስት የሚመራ ፖለቲካዊ ትርኢት አይደለም ብለዋል፡፡

“ያ ብሔራዊ ምክክር አካታች፣ ለአሳታፊነት እንዲመች ለሁሉም ክፍት እንዲሁም ቀውሱን ያስከተሉት መልከ ብዙ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት የእውነተኛ ውይይት መድረክ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን [ይህ ውይይት] የተቀረጸበት መንገድ መግፍኤው ስልጣንን ማጠናከርና ለመጻኢ ምርጫ በፖለቲካዊ ሒደት የመንግስቱን ቅቡልነት ማጠናከር እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህም እውነተኛ ብሔራዊ ምክክር አይደለም፤ የፖለቲካ ፕሮጄክት ነው፡፡ ብሔራዊ ምክክር ከሆነ አካታች እና አሳታፊ መሆን አለበት”ብለዋል፡፡

ንያንዴንግ ብሔራዊ ምክክርን በኃሳብ ደረጃ ቢቀበሉትም፣ አሁን ያለውን ሒደት ሁሉን አካታች ያለመሆን ሞግተዋል፡፡

“ሌሎች ሰዎችን፣ የተለየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ማካተት ካልፈለግህ፣ ከማን ጋር ነው ምክክር ማድረግ የምትሻው? ከጓደኛህ ጋር አይደለም? ከጓደኛህ ጋር ከሆነ ደግሞ ይህ ብሔራዊ ምክክር አይደለም፡፡ ግለ መነባንብ ነው፤ ምክንያቱም ጓደኞችህ የተለየ ምልከታን ሊያቀርቡልህ አይችሉም፤ እና ይህ ምክክር ውጤታማ ይሆናል ብየ አላስብም፤ ምክንያቱም ማንም ሰው ከጓደኛው ጋር ሆኖ ሰላምን ሊያመጣ አይችልም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የቀጠናው መሪዎች እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የደቡብ ሱዳን መንግስት ጦርነቱን እንዲያቆምና እ.ኤ.አ. የ2015ቱን የሰላም ስምምነት በተፈረመበት መልኩ እንዲያከብር ጫና በማሳደር በአንድ ድምጽ እንዲናገሩ ወትውተዋል፡፡ ሪቤካ በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት፣ የሰላም ሒደቱን በመመለስ እና ገደብ አልባ ሰብዐዊ ተደራሽነትን በማስጠበቅ ላይ አትኩሮት እንዲደረግ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡

17799048_1001257060009718_4171461174072050338_n-2

“እናት እንደመሆኔ ድምጼን የማሰማት እና ይህ ግጭት እንዲቆም የመጎትጎት ኃላፊነት አለብኝ፡፡ ሴቶቹ እየተሰቃዩ ነው፣ እየሞቱ ነው፣ እየተደፈሩ ነው፡፡ ምግብ የላቸውም፤ መጠለያ የላቸውም፡፡ በጦርነት  ምክንያት ልጆቻቸው ወደትምህርት ቤት መሄድ አቁመዋል፡፡ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ከመጥፎው ወደባሰው እየሄደ ነው፡፡ ቀጠናው አንድ ላይ መሆንና ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ያለውን አቅም ሁሉ መጠቀም አለበት፡፡”

ሪቤካ ንያንዴንግ ራሳቸውን ‘የአገሪቱ እናት’ ሲሉ ጠርተዋል፡፡ ሟቹ ባለቤታቸው እ.ኤ.አ. በ1983 የተመሠረተው አማጺ ቡድን ቆይቶም ከ(ሰሜን) ሱዳን መንግስት ጋር እ.ኤ.አ በ2005 በካርቱም ከተደረሰው የሰላም ስምምነት በኋላ የመጀመሪያው የደቡብ ሱዳን ገዥ ፓርቲ የሆነው የኤስፒኤልኤም የመጀመሪያ ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ ከታህሳስ 2013 ጀምሮ ኤስፒኤልኤም ወደሁለት ተፎካካሪ አንጃዎች ተሰንጥቋል፡፡ ንያንዳንግ የትኛውንም ታጣቂ ቡድን መደገፍን ትተው፣ ትጥቅ አልባ ከሆነውና ‘የኤስፒኤልኤም ጂ10’፣ ‘የቀድሞ ታሳሪዎች’ ወይንም ‘የኤስፒኤልም መሪዎች’ በሚሰኙ ተቀያያሪ ስሞች ከሚጠራው ሦስተኛ ስደተኛ ቡድን ጋር ራሳቸውን አያይዘዋል፡፡ በተቃራኒው ልጃቸው ማቢዮር ጋራንግ ታጣቂውን ኤስፒኤልኤም-አይኦ በቃል አቀባይነት ተቀላቅለዋል፡፡

የመንግስት ባለስልጣናት የታቀደው ብሔራዊ ምክክር ተቃዋሚዎችን ያገልላል እንዲሁም ዓላማውን የመንግስትን ስልጣንን ማደርጀት ያደረገ ነው የሚለውን አስተያየት አይቀበሉም፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ብሔራዊ ምክክሩን በገንዘብ እንዲደገፍ ይፈልጋሉ፡፡

የፕሬዚዳንቱ የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ ቱት ኪው ጋትሉክ በፖለቲካዊ ሒደቱ የሚመለከታቸውን አካላት በሙሉ በማካተት ዘላቂ ሰላምን ለማስገኘት ተግባራዊ እርምጃዎች መውሰዳቸውን በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል፡፡ ቱት ከተባበሩት መንግስታት፣ ከቀጠናው አባላት እና ከሰፊው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጋር ትብብር እንዳለ ይጠቅሳሉ፡፡ መንግስት “ከአሉታዊ ዘመቻ ይልቅ” ጥረቱ እውቅና እንደሚሰጠው እንደሚጠብቅም ተናግረዋል፡፡

የፕሬዚዳንቱ አማካሪ የጅምላ ጭፍጨፋ ውንጀላዎችንም አጣጥለዋል፡፡ ደቡብ ሱዳን የተለያዩ ሕዝቦች በሰላም የሚኖሩባት፣ ብዝሃነት የሞላባት አገር መሆኗን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ ባለስልጣኑ ግጭቱንም የዘር ይዘት የሌለው ፖለቲካዊ ብቻ ነው ብለውታል፡፡

ቱት የመንግስት ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ አድርገዋል ወይንም ወሲባዊ ጥቃትን እንደጦርነት ስልት ተጠቅመዋል የሚለውን አስተያየት ያጣጣሉ ሲሆን መንግስት ልክ እንደሌሎች አገራት ሁሉ የጸጥታ ስጋት ባገጠመ ጊዜ ራሱን እየተከላከለ እንደነበር አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡ መንግስቱን ማነቃነቅን ብቸኛ ዓላማቸው ያደረጉ ታጣቂ ቡድኖች በፖለቲካዊ ጥቅም ፈላጊዎች እና በወንጀለኞች እየተቋቋሙ ናቸውም ብለዋል፡፡ ለጥቀውም ለተከሰተው ረሃብ ተጠያቂው መንግስት ነው የሚለውን ውንጀላ ውድቅ አድርገው፣ ማዕቀቦች እና የጦር መሣርያ ዝውውር እገዳዎች ውጥረቶችን እንደሚያባብሱ አስምረዋል፡፡

c9jzqi3waaesmc7-3
ዩዌሪ ሙሴቪኒ ቁልፍ የሳልቫ ኪር አጋር ከሆኑት ከደቡብ ሱዳኑ ታባን ዴንግ ጋር

ይህ በእንዲህ እንዳለ የደቡብ ሱዳን መንግስት ለንያንዴንግ እና ሌሎች የኤስፒኤልኤም ስደተኛ መሪዎች ጉብኝት ምላሽ በሚሆን መልኩ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ታባን ዴንግን ከሙሴቬኒ ጋር እንዲገናኙ ወደዩጋንዳ ልኳል፡፡ “ሁሉም የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ከነውጥ እንዲታቀብ እጠይቃለሁ፡፡ ልማትን ለማሳካት ብቸኛው አዋጭ መንገድ ሰላም እና ውይይት ነው” ብለዋል ሙሴቪኒ በማኅበራዊ የብዙሃን መገናኛ ከውይይቱ በኋላ፡፡ ቀደም ሲል ከሪቤካ ንያንዴንግ እና ከልዑካን ቡድናቸው ጋር ለመገናኘታቸው ማረጋገጫ የሰጡ ሲሆን ውይይቱ “በደቡብ ሱዳን ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችን እንደምን ማዋኻድ ይቻላል በሚለው ዙርያ” እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ ሙሴቪኒ እ.ኤ.አ. 2014-2015 ኪር ያደረጉትን ጸረ-አማጽያን እንቅስቃሴ፣ የጆንግሌይን ግንባር ለመያዝ የጦር ኃይል በማዋጣት ደግፈው የነበረ ቢሆንም፣ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ግን የጦር ኃይላቸውን አውጥተዋል፡፡ በቀጠለው የብጥብጥ ስርጭት የተነሳ ወደዩጋንዳ ከፍተኛ የሆነ ስደተኛ እያቀና ይገኛል፡፡