በሞቃዲሾ የሚገኙት የዩኤስ ጦር አባላት የሎጅስቲክስ ባለሞያዎች ናቸው- የአፍሪኮም አዛዥ

US Africom Commander Thomas D. Waldhauser

የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ሠራዊት ቀደም ሲል በዚህ ወር በሶማሊያዋ መዲና ሞቃዲሾ የተራገፈው የአሜሪካ ወታደሮች ቡድን የሎጅስቲክ እንጅ የፍልሚያ ሚና የለውም በማለት የክስተቱን ፋይዳ እያቃለለው ይገኛል፡፡

የዩስ እዝ በአፍሪካ (አፍሪኮም) አዛዥ የሆኑት ጄነራል ቶማስ ዋልድኻውዘር ባለፈው ሐሙስ የወታደሮቹ ወደሶማሊያ መምጣት “ዘወትራዊ” እና የረጅም ዕቅድ የስልጠና ትግበራ አካል መሆኑን ለጋዜጠኞች በስልክ ባደረጉት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

“ወደሶማሊያ የተላኩት ወታደሮች በእርግጥም ጊዜያቸው ተቋም ግንባታ በምንለው ተግባር ላይ የሚያሳልፉ የሎጅስቲክ ባለሞያዎች ሲሆኑ፣ የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ኃይል የአቅርቦት መስመር መዘርጋትን፣ ክፍሎች መኖራቸውን እንዲሁም እርምጃዎች በትክክል አቅርቦት እየደረሳቸው መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስልጠናዎችን ይሰጣሉ” ብለዋል፡፡

ዋልድኻውዘር አክለውም  “ይህ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሲሠራበት የቆየ ዘወትራዊ ወታደሮችን የማምጣት ክንውን አካል ነው… እነዚህ ልዩ ልዩ ተቋማትን፣ የሶማሊያ ብሔራዊ ጦርን በአቅርቦት ብሎም ቁሳቁሶችን በመቆጣጠር ረገድ እና በመሳሰለው የተሻሉ እንዲሆኑ እገዛ የሚያደርጉ የሎጅስቲክ ባለሞያዎች ናቸው” ብለዋል፡፡

አሜሪካዊው አዛዥ ከዚህም ባሻገር የወታደሮቹ መጥተው መራገፍ የተናጠል እርምጃ ሳይሆን የሶማሊያ የጦር ኃይልን ለማሳደግ የሚደረግ ሰፋ ያለ ዓለም አቀፋዊ ጥረት አካል መሆኑን አስምረውበታል፡፡ “ቱርክ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ዩናይትድ ስቴትስ (እና) አሚሶም ሁሉ ስልጠና ይሰጣሉ፡፡ ስለዚህ የጋራ ጥረት ነው” ብለዋል ዋልድኻውዘር፡፡ “የሶማሊያ የጦር ኃይል የአገሪቱን የደህንነት ሁኔታ በራሳቸው ለመቆጣጠር የሚያስችለው ቁጥር ላይ ይደርስ ዘንድ የሚደረግ የጋራ ጥረት ነው፡፡”

ይሁንና ሌላ የዩኤስ የጦር ኃይል ባለስልጣን ለአሜሪካ ድምጽ በቅርቡ እንደተናገሩት የሥራ ግባቸው ከሎጅስቲክስም የሚዘልል ወደ 50 የሚጠጉ የአሜሪካ ጸረ-ሽብር አማካሪዎች በአሁኑ ሰዐት ሶማሊያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

የዩኤስ እዝ በአፍሪካ ቃል አቀባይ የሆኑት ቻርልስ ቸክ ፕሪቻርድ በቁጥር “ጥቂት ደርዘኖች” የሚሆኑት ተጨማሪ የሎጅስቲክ ባለሞያዎች- ከ101ኛው የአየር ወለድ ክፍለ ጦር- ወደ ሞቃዶሾ መምጣታቸው የሶማሊያ መንግስትን ጥያቄ ተከትሎ የተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (አሚሶም) የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ አምባሳደር ፍራንሶስኮ ማዲዬራ እ.ኤ.አ. ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የዓለም አቀፍ ጦር ኃይላት አባላትን ከሶማሊያ የማስወጣቱን ዕቅድ ደገመው አውስተዋል፡፡

“ከሶማሊያ መውጣትን እ.ኤ.አ በ2018 መጀመር ዕቅዳችን ነው፡፡ ምክንያቱም ጄነራል ዋልድኻውዘር እንዳሉት እዚያ እስከዘላለሙ የመቆየት ዕቅድ አልነበረንም፣ የለንምም፡፡ ሶማሊያ ለሶማሊያውያን ናት፡፡ እኛ እንደሌሎቹ አፍሪካውያን ሁሉ የየራሳችን አገራት አሉን፡፡ ከሶማሊያውያን ጋር አብረን ነን፤ ሶማሊያውያንን ማገዝ ያሻናል፡፡ የተረጋጋች ሶማሊያን መኖር ፍላጎታችን ነው” ብለዋል ወኪሉ፡፡

“ነገር ግን በእርግጠኛነት አገሪቱ ከማንም በተሻለ ሁኔታ ልትጠበቅ የምትችለው የራሳቸውን መስተጋብር፣ የራሳቸውን እውነታ፣ የራሳቸውን ተቀዳሚ ፍላጎቶች እና ዓላማዎች በሚያውቁ ሶማሊያውያን ፣ በራሳቸው በሶማሊያውያን ነው፡፡ ስለዚህ የሆነ ጊዜ ላይ ለቅቀን መሄድ ይኖርብናል” ሲሉ ማዲዬራ አክለዋል 2018 አገሪቷን ለቅቆ መውጣቱ የሚጀመርበት ጊዜ መሆኑን ደግመው አጽንዖት በመስጠት፡፡