ከደቡብ ሱዳን የአፐር ናይል ወታደራዊ ጥቃት ጀርባ ያሉ አምስት ፖለቲካዊ ጉዳዮች

(ከኮዶክ እና ቶንጋ የሰላማዊ ዜጎችን መፈናቀል የሚያሳይ የተባበሩት መንግስታ ድርጅት ካርታ)

እ.ኤ.አ. በወርሃ ሚያዝያ መገባደጃ እና በግንቦት መጀመርያ ላይ በደቡብ ሱዳኗ አፐር ናይል ግዛት፣ ኤስፒኤልኤ በመባል የሚታወቀውን መንግስታዊውን የጦር ኃይል የኤስፒኤልኤም/ኤ አማጺ ቡድን አካል ከሆነው እና አጉሌክ ከሚሰኘው በዋነኛነት የሺሉክ ጎሣ አባላትን ካከተተው ታጣቂ ቡድን ጋር ያላተመ ከባድ ፍልሚያ ተቀጣጥሏል፡፡

ከሥፍራው የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት እ.ኤ.አ. በግንቦት መጀመሪያ ላይ ኤስፒኤልኤ የቶንጋ እና ኮዶክ አካባቢዎችን ተቆጣጥሯል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ባለስልጣናት የፍልሚያውን ሰብዐዊ መዘዝ በማውሳት፣ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የሺሉክ ጎሣ አባላት የሚገሰግሰውን የመንግስት ጦር ሽሽት ወደሱዳን ወይንም አቡሮክ ውስጥ ወደሚገኝ የተፈናቃዮች መሥፈሪያ መሰደዳቸውን፣ በርካቶቹም በጉዞ ላይ ሳሉ ከፈሳሽ እጥረት እና ከድካም የተነሳ ሕይወታቸው ማለፉን ይናገራሉ፡፡

“በአቡሮክ የሚገኙ ሰላማዊ ዜጎች ከባድ እና ቅርብ ለሆነ የከፍተኛ የሰብዐዊ መብቶች ጥሰት፣ ለጎሣ ግጭት እና ዳግመኛ ከሠፈራው ለመፈናቀል ስጋት ተጋልጠዋል” ብለዋል የተባበሩት መንግስታት የሰብዐዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራዓድ አል ሁሴን እ.ኤ..አ. ግንቦት 4 ቀን፡፡

ከአሁኑ ወታደራዊ ግጭት ጀርባ ያሉት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ግን ብዙም ውይይት ሲደረግባቸው አይስተዋልም፡፡ ከጀርባው ምን አለ? በቅርቡ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የብሔራዊ ምክክር ውጥን ይፋ ከመደረጉ በተቃራኒ ለምንድን ነው መንግስት ጥቃት በመሠንዘር ላይ የሚገኘው?

ዘ ሜሴንጀር ታብራራለች፡-

1. ቅቡልነትን ፍለጋ የሚደረግ መውተርተር

አዲሱ ወታደራዊ ጥቃት ለመንግስቱ ታማኝ የሆኑ የሺሉክ ጎሣ አባላትን የሚጠቅም ነው፤ ወደቀያቸው መጓዝ ያለመቻላቸው ሊደርሱበት ያልቻሉትን አካባቢ በመወከል እንግዳ ሁኔታ ውስጥ ከትቷቸው የቆየ ሲሆን፣ ቅቡልነታቸው እና ለመንግስቱ ያላቸው ጠቀሜታ ላይ ጥያቄ አጭሯል፡፡ ታማኙ ቡድን በቅርቡ በዌስተርን ናይል ግዛት ካቢኔ ውስጥ የተሰየሙ ሹመኞችን ያካትታል፤ ካቢኔው የሳልቫ ኪርን ‘የምሥረታ ትዕዛዝ’ ተከትሎ የተዋቀረ ነው፡፡ ከመንግስቱ ታማኞች መካከል በቅርቡ ዳግመኛ የከዱትን ቲጁዎክ አጉየትን ጨምሮ አንዳንድ ብሔራዊ ፖለቲከኞች ይገኙበታል፡፡

በሺሉክ አካባቢ ላይ የመንግስቱ ጦር አንድ ጊዜ ወታደራዊ ይዞታን ከመሠረተ በኋላ፣ የዌስተርን ናይል መንግስት በስደት ከጁባ እና ከማላካል ሆኖ ማስተዳደሩን ትቶ ዋና መቀመጫውን ወደኮዶክ መውሰድ ይቻለዋል፡፡ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት መንግስት ውስጥ ያሉ አንዳንድ የሹሉክ ባለስልጣናት ኮዶክን ነጻ ለማውጣት ከኤስፒኤልኤ አካባቢያዊ እዝ ጋር ተባብረዋል፡፡ የሹሉክ ጎሣ አባል የሆኑ አንድ የመንግስት ባለስልጣን ይህንን ለዘ ሜሴንጀር በላኩት ኢሜል ያረጋገጡ ሲሆን፣ የቅርብ ሹመኞቹ “መሬት ላይ  የግዛታቸውን ስልጣን ለማጠናከር እየተዋጉ ናቸው” ብለዋል፡፡

“የጁባው መንግስት ቅቡልነቱን ለማስቀጠል መሬት ላይ ተግባራዊ ሁኔታን በወታደራዊ ኃይል ማስፈን ይሻል፡፡ ከቅርቡ የፕሬዚዳንት ኪር ሕገ መንግስታዊ ሹመት አሰጣጥ የተጠቀሙት ናቸው ጁባ ላይ ላለው ሿሚ አካል ብርቱ ታማኝነትን እያሳዩ ያሉት፤ መሬት ላይ የግዛታቸውን ስልጣን ለማጠናከር እየተዋጉ ናቸው” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ሌላኛው መንግስት ውስጥ ያሉት የሺሉክ ተወላጅ ባለስልጣን የግብርና ሚኒስትሩ ኦንዮቲ አዲጎ ዳግም ግጭት ለመቀስቀሱ አማጽያንን እና ዓለም አቀፍ የተኩስ አቁም ተቆጣጣሪዎችን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ግንቦት ከሜሰንጀር ጋር ባደረጉት የብቻ ቃለ መጠይቅ “የሰላም ስምምነቱን በመተግበር  ረገድ ችግር አለ፤ ይህም በአገሪቱ ውስጥ ሥር ሰድዶ እየተዛመተ ያለውን ቀውስ በመግታት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስኬታማ ያለመሆኑን በግልጽ ያሳያል.. ኩዶክ ውስጥ፣ አቡዎክ ውስጥ እና በሌሎች ሥፍራዎችን ያለው ክስተት የጄኤምኢሲ (የጋራ ቁጥጥር እና ግምገማ ኮሚሽን) ሥራ ነው፣ የተኩስ አቁም እና የሽግግር የደህንነት ክንውን ቁጥጥር ስልቶችን በመጠቀም የተከሰተውን ነገር ማረጋገጥ እና መዘገብ ይኖርበታል፡፡”

መንግስቱን ከመቀላቀላቸው በፊት በአንድ ወቅት የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባል የነበረ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ጥምረት የተሰኘ ተቃዋሚ ቡድንን ይመሩ የነበሩት ኦንዮቲ በቅርቡ በአፐር ናይል የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ምን እንደቀሰቀሰው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ነው ይህንን ያሉት፡፡

2. የሳል ኪር ትዕዛዛት

5335499393_9ccac19739_b.jpg
አፐር ናይል እና ሺሉክ ውስጥ ያሉ የኤስፒኤልኤ ባለስልጣናት ብቻቸውን እርምጃዎቻቸውን የሚወስዱት ብቻቸውን አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ለግዛት ገዥዎች በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ሥር ያሉ ሆኑ አልሆኑ ለየግዛቶቹ ዋና መስሪያ ቤቶች ሪፖርት እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ያስተላለፉትን የሳልቫ ኪርን ትዕዛዝ እየተገበሩ ነው፡፡

የአሁኑ ወታደራዊ ጥቃት ጥንስስ ኪር እ.ኤ.አ በ2015 ያስተላለፉት ‘የምሥረታ ትዕዛዝ’ ነው፤ ይህም ትዕዛዝ የአፐር ናይል ግዛትን አፍርሶ ወደሦስት ግዛቶች ከፋፍሎታል፡፡ ሁለት ወራትን ቀደም ብሎ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ላይ ያለ አንድ አንቀጽን መተግበር ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ ስምምነቱ የአፐር ናይልን የማስተዳደርን ኃላፊነት ለአማጺው ኤስፒኤልኤም-አይኦ አስተላልፏል፡፡

ግዛቱን ወደትንንሽ አስተዳደራዊ አሃዶች በመከፋፈል በእነዚህ አካባቢዎች ሊኖር የሚገባውን የአማጺውን ቡድን የማስተዳደር ስልጣን ጉዳይ ገለል አድርገው በአዳዲሶቹ የአስተዳደር ክፍሎች የራሳቸውን ታማኝ ሰዎች ለማስቀመጥ አስችሏቸዋል፡፡ አማጽያን በያዙት የሹሉክ ቀጠና ውስጥ የምትገኘውን ኮዶክን የአዲሱ የዌስት ናይል ግዛት መዲና አድርገው የሰየሙ ሲሆን፣ በዚህም በዘወርዋራ ለወታደራዊ ጥቃት ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ኪር በቅርቡ አዳዲስ ሹመኛ የግዛት አስተዳዳሪዎች የሚያስተዳድሯቸው ግዛቶች በአማጽያን የተያዙ ሆኑም አልሆኑ ዋና መስሪያ ቤታቸውን እንዲይዙ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ የኮዶክ መያዝ ኪር ያወጡት ስልት እና የሰጧቸው ትዕዛዛትን  ተፈጻሚ መሆን ያመላከተ ሆኗል፡፡

3. ሰፊ ወታደራዊ ስትራቴጂ

የአፐር ናይሉ ወታደራዊ ጥቃት ዝናባማው ወቅት ከመጀመሩ በፊት በአማጽያን ላይ ስልታዊ የበላይነትን ለመያዝ በበርካታ ግንባሮች ከተያያዘው ሰፊ የኤስፒኤልኤ ወታደራዊ ጥቃት ጋር አብሮ የሚሄድም ነው፡፡

ለምሳሌ ያህል በሌሎች የአፐር ናይል አካባቢዎች በኤስፒኤልኤ እና  ኤስፒኤልኤ-አይኦ መካከል ካሉ ግጭቶች መካከል በሶባት ወንዝ መተላለፊያ በቹይል እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 23 ቀን የነበረው ግጭት ወንዙን የእንቅስቃሴ መተላለፊያ አድርጎ የመጠቀምን ተግባራዊ ዓላማን የሚጠቁም ነው፡፡ ይህም ጠንካራ የመንግስት ይዞታ የሆነችውን ማልካልን ናሳር ውስጥ ካለው ትንሽ የጦር ሠፈር ጋር የሚያገናኝ ይሆናል፤ በዚህም የጦር ሠፈሩን በመጭዎቹ ዝናባማ ወራት አቅርቦት ማድረስን ቀላል ያደርገውና አማጽያኑን ይበልጡኑ ወደኢትዮጵያ ይገፋቸዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በስተደቡብ ራቅ ብሎ ባለፈው ወር በዋኣት እና በዋልጋክ የተከሰቱት ግጭቶች መንግስት በደረቅ ወቅት የሚያደርጋቸውን ጥቃቶች መጠናከር ያሳያሉ፤ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት ከዚያን ጊዜ አንስቶ ኤስፒኤልኤ ዝናብ ባጨቀየው መንገድ እንዳይደናቀፉበት ከባድ የጦር መሣርያዎችን ወደ ዩዋይ አጓጉዟል፡፡ የዝናባማ ወቅት ለአማጽያን ሥፍራዎቹን መልሰው እንዲይዙ የሚመቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡

የአሁኑ ጥቃት ወታደራዊ አመክንዮ ከመጥፎ ምጣኔ ሐብታዊ እና ሎጅስቲካዊ ሁኔታዎች የሚነሳም ነው፡፡ የኮዶኩ ጥቃት በተወነጨፈበት በናይል ወንዝ ምስራቃዊ መፋሰሻ የሚገኙ የኤስፒኤልኤ የጦር አዛዦች የተጋነነ የዋጋ ግሽበትን፣ የሕዝብ ሽሽትን እንዲሁም በናይል ወንዝ ላይ በሚካሄደው የንግድ ልውውጥ የደህንነት ስጋትን ተጋፍጠዋል፡፡ በኮዶክ አቅራቢያ ያለውን ምዕራባዊውን የወንዙን መፋሰሻ መያዝ እና መቆጣጠር ምግብ እና ሌሎችንም አቅርቦቶች በቀላሉ እንዲያገኙ ሲያስችላቸው በናይል ወንዝ ላይ ያለውን ዝውውር ደህንነት በተሻለ አኳኋን ለማስጠበቅ ያስችላቸዋል፡፡

ለዚህ ጽሑፍ ጥንቅር ጥያቄ የቀረበላቸው የመንግስት ውስጥ አዋቂ እንደሚሉት ከሆነ “ለኪር መንግስት ተጠቃሚነት ሲባል ከሬንክ እስከ ጁባ ያሉትን የናይል መንገዶች መቆጣጠርም ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡ የአየር መጓጓዣ ስኬታማ ባለመሆኑ ዱራ (ማሽላ) ከሬንክ መጋዘኖች ወደ ጆንግሌይ፣ ባህር ኤል ጋዛል እና የኢኳቶሪያ አካባቢዎች ከኗሪዎችም ሆነ ለወታደራዊ ግብዐት ለማቅረብ ጫና አለ፡፡”

አሁን ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ጊዜ ሁሉ የኤስፒኤልኤ ኃይሎች ራሳቸውን ማዛለቅ የቻሉት የአጥቢያ ግብር በመጣል እና በያዟቸውን አካባቢዎች የሚገኙ ግብዐቶችን በመውሰድ ነው፡፡ የሺሉክ ቀጣናን መቆጣጠር የገቢ ዕድሎችን ይፈጥራል “በተለይ ደግሞ ሙጫ፣ ከሰል፣ ዓሣ በሰሜን-ደቡብ ንግድ ከሚዘዋወሩ አርብቶ አደር አረብ ነጋዴዎች የሚገኝ ቀረጥን፤ ይህም የጁባውም ሆነ የየግዛት መንግስታቱ ማባሪያ በሌለው ክፍፍል እና በነዳጅ ገቢ ማነስ ምክንያት የገንዘብ እጥረት ካዝናውን ራቁት ያስቀረውን መንግስታቸውን ለመደጎም ይፈልጉታል” ሲሉ ውስጥ አዋቂው ለዘ ሜሴንጀር ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው መጋቢት ፕሬዚዳንት ኪር የተኩስ አቁም ስምምነት ለማወጅ ቆርጠዋል የሚሉ ዘገባዎች ያልተረጋገጡ ሲሆኑ ምናልባትም ከሀሰተኛ ዲፕሎማቲካዊ ምንጮች የተነሱ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ኪር አንዳችም የግጭት ማቆም እወጃ አልለቀቁም፡፡ በተቃራኒው የመንግስታቸው ቃል አቀባይ እ.ኤ.አ.  ግንቦት 3 ቀን መንግስት “የተኩስ አቁም ስምምነት መደንገግ አይችልም” ሲሉ አክለውም “የሰላም ስምምነቱን መልሶ መተግበር የሚያልም ሰው፣ ያንን ህልም መከለስ ይኖርበታል” ብለዋል፡፡

dsc_0904-2

እንዲህም ሆኖ ግን ቃል አቀባዩ ይህንን ባሉ በማግስቱ የተባበሩት መንግስታት የሰብዐዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን “ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እ.ኤ.አ. መጋቢት 25 ቀን ብቻቸውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማወጅ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ” መንግስታቸውን ወትውቷል፡፡ በተናጠልም የጋራ ቁጥጥር እና ግምገማ ኮሚሽኑ ተቆጣጣሪዎች የአገሪቱን መንግስት በጦር ኃይሉ ላይ የበላይነት እና ቁጥጥር እንዳለው እንዲያስረዳ ጠይቀዋል፤ መንግስትም አለኝ ሲል ምላሹን ሰጥቷል፡፡

4. ሰብዐዊ እርዳታን መቆጣጠር

የመንግስት ኃይሎች እና አማጺያኑ በእኩል ደረጃ ለረሃብ በቀረቡ ሁኔታዎች፣ ከፍ ባለ ግሽበት እና ሎጅስቲካዊ እንቅፋቶች ውስጥ እየታገሉ ይገኛሉ፤ በተመሳሳይ ጊዜም የእርዳታ እንቅስቃሴዎች፣ በሺሉክ ቀጠና ምዕራባዊ የናይል ዳርቻ ጭምር በአግባቡ የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረግላቸው ናቸው፡፡
የምጣኔ ሐብት ምንጮች ሲስለመለሙና የመንግስት የአቅርቦት ሥርዓት ሲሰናከል፣ የኤስፒኤልኤ ኃይሎች የዓለም አቀፍ የእርዳታ እንቅስቃሴዎችን በዝርፊያ እና በቀረጥ አማካይነት የገቢ እና የምግብ ምንጭ ወደማድረግ ዞረዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በወርሃ ግንቦት የመጀመሪያ ሳምንት የሰብዐዊ እርዳታ ባለሞያዎች በቀደመው ሳምንት በአፐር ናይል በነበረው ነውጥ “ቁልፍ የሰብዐዊ እርዳታ ንብረቶች ተዘርፍዋል” ያሉ ሲሆን በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጊዜያው አስተባባሪ ሰርጅ ቲሶት ግን ለዝርፊያው ተቃዋሚ ኃይሎችን እና “ሌሎች አካላትን” ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በወርሃ ሚያዝያ የመጨረሻው አርብ በተደረገው የካቢኔ ስብሰባ ላይ የሰብዐዊ እርዳታ መስጫ ሥፍራዎችን የመቆጣጠር ጉዳይ በግልጽ ለውይይት ቀርቦ እንደነበር አንድ የካቢኔ ሚኒስትር ይናገራሉ፡፡

የሺሉክ ጎሣ አባል የሆኑት የግብርና ሚኒስትሩ ኦንዮቲ አዲጎ የመንግስትን ጥቃት ምክንያት ሲያብራሩ “ነፍጥ ያነገቡ በአካባቢው ያሉ የማቻር ኤስፒኤልኤ-አይኦ አባላት የኤስፒኤልኤ ኃይል ይዞታዎችን ማጥቃታቸውን እና ለሰላማዊ ዜጎች ሰብዐዊ እርዳታ እንዳይደርስ መከልከላቸውን የሚናገሩ ዘገባዎች አሉ፡፡ ባለፈው አርብ የመከላከያ ሚኒስትሩ፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትሩ ለካቢኔው የተናገሩት ያንን ነው፡፡”

ስለዚህም ለጥቃቱ የሚቀርበው የሰብዐዊ እርዳታ አመክንዮ በመንግስት ትርክት ውስጥ የአማጽያኑ ጥቃት ተመጣጣኝ አጸፋ ያስፈልገዋል ከሚለው ለጥቆ ዐብዩ ሆኖ ይስተዋላል፡፡

5. የተቃዋሚው ኃይል መበታተን

“ጁባ ከዚህም ባሻገር መሬት ላይ በተለይ በአግዌሌክ አካባቢ ባሉት የኤስፒኤልኤም-አይኦ ኃይሎች የሚስተዋለውን የእዝ መበጣጠስ እና የሞራል መውደቅ እየተጠቀመችበት ትገኛለች” ይላሉ ሌላኛው የሺሉክ ተወላጅ የመንግስት ውስጥ አዋቂ፡፡

አጉዌሌክ ተብሎ በሚታወቀው በጄኔራል ጆንሰን ኦሎኒ አንጃ እና በሌሎቹ ፖለቲካዊ እና ታጣቂ ቡድኖች፣ ለምሳሌ በላም አኮል በሚመራው ብሔራዊ ዲሞክራሲያው ንቅናቄ እንዲሁም ከኤስፒኤልኤ ጥቃት በፊትም ከኦሎኒ ቡድን ባገጠመው ውስጣዊ ግጭት “ከፊል መፈራረስ” ባገጠመው በአዲስ የነብሮች ግንባር መካከል ያሉትን ልዩነቶችም ይጠቁማሉ፡፡

የመንግስቱ አዲስ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ተቃዋሚዎች ውስጣዊ ቅራኔዎቻቸውን ከመፍታት እና በሺሉክ ግዛት ራሳቸውን ከማጠናከር የሚያሰናክሉ ናቸው፡፡ ባለስልጣኑ እንደሚሉት ከሆነ ዋነኛው ግብ “ተቃዋሚ ኃይሎች አሁን ላለው በአንድ ኤስፒኤልኤም ሥር ለመዋሃድ እና እ.ኤ.አ በ2018 ምርጫ ለማካሄድ ለወጠኑት ባለሦስትዮሽ የኪር-ታባን-ኢጋ ጥምረት ሕልውናዊ ስጋት በማይደቅን መልኩ በፋይዳ ቢስነት ስደተኛ ሆነው ይኖሩ ዘንድ የድጋፍ መሠረትን መከልከል ነው፡፡”

dscf1228-2

የዚህ ሁኔታ ሌላኛው ቁልፍ አሸናፊ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ታባን ዴንግ ጋይ ሲሆኑ እርሳቸውም ስልጣናቸው የኤስፒኤልኤም/ኤ-አይኦ አመራር ነኝ ከማለታቸው የሚመዘዝ ነው፡፡ እውነታው ግን ታባን የአማጺው ቡድን ውስጥ አነስተኛ የሰላም ክንፍን የሚመሩ መሆኑና የቀሪዎቹ በጆንግሌይ፣ በዩኒቲ እና በአፐር ናይል ግዛቶች ያሉ አማጺ ወታደሮች ታማኝነት የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ እየተካሄደ ያለው የአፐር ናይል ጥቃት የሺሉክ ቀጠና የታባንን መሪነት ከማይቀበሉ እና ከእርሳቸው ይልቅ ከተፎካካሪያቸው ሪች ማቻር ጋር ራሳቸውን ከሚያሰልፉ  ከ‘አጉዌሌክ’ ኤስፒኤልኤም/ኤ-አይኦ ኃይሎች ነጻ መውጣታቸውን ለማረጋገጥ የሻተ ነው፡፡