ጀርመናዊው ምሁር የአገራቸውን የአፍሪካ ፖሊሲ ወጥነት ይጎድለዋል ሲሉ ተቹ

የጀርመን ፌዴራላዊ መንግስት የምጣኔ ኃብት ትብብርና የልማት ሚኒስትር ገርድ ሙለር

በጀርመን የአፍሪካ ጉዳዮች ተቋም የታተመ አዲስ ሪፖርት የጀርመን ፌዴራላዊ መንግስት ለአፍሪካ ያለውን የውጭ ፖሊሲ ነቅፏል፤ ሪፖርቱ የጀርመን የልማት እርዳታ የአፍሪካን ግብርና የሚጎዳው የአውሮፓ የግብርና ፖሊሲ ጥላ ያጠላበት ነው ብሏል፡፡

“አዳዲስ አድማሶች ለጀርመን የአፍሪካ ፖሊሲ” የሚል ርዕስ ያለውና የጀርመን ዓለም አቀፍና አካባቢያዊ ጉዳዮች ተቋም (ጊጋ) አባል በሆኑት ሮበርት ካፐል የተጠናቀረው ሪፖርት ጀርመን ለ‘አምባገነን’ መንግስታት የምትሰጠው ድጋፍ ላይ ጥያቄ ያነሳ ሲሆን፣ ይህም አገሪቱ እከተለዋለሁ ከምትለው ‘እሴት-ተኮር ፖለቲካ’ ጋር አብሮ የማይሄድ ነው ይላል፡፡

በጊጋ ከፍተኛ የምርምር ፌሎው እና የኃሳብ አመንጭ ተቋሙ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የሆኑት ካፐል ያቀረቡት ነቀፌታ በጀርመን የልማት ሚኒስትር ገርድ ሙለር እ.ኤ.አ በጥር 2017 በተለቀቀቀው ባለ33 ገጽ ‘ጠቅላይ ዕቅድ’ (ማርሻል ፕላን) ለአፍሪካ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡

‘ጠቅላዩ ዕቅድ’ ጀርመን አፍሪካ ውስጥ በትምህርት፣ በንግድ፣ በቢዝነት ልማት፣ በኃይል አቅርቦት እና በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ ለምታደርገው የልማት የገንዘብ ድጋፍና የግል ኢንቨስትመንት የፖሊሲ ፍኖተ-ትልም ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ ካፐል እንደሚሉት ዕቅዱ በጀርመን-አፍሪካ ግንኙነት ያለውን “የኃይል ሚዛን ፖለቲካ” ሃቀኛ በሆነ አግባብ ሳያጤን፣ ጀርመንን ለጋሽ የአፍሪካ ቤዛነት ሚና አላብሷታል፡፡

“የምጣኔ ኃብት ትብብር እና የልማት ሚኒስትር የደጉ ሳምራዊን ገጽታን አራግፎ፣ በፍላጎቶቹ እና ሲቪል ኃይል በመሆን ፖለቲካዊ ቅኝት መመራት ይፈልጋል፡፡ ይህ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ጽንሰ ኃሳቡ ከደጉ ሳምራዊ እሳቤ ጋር ተቀይጦ፣ የጀርመንን የኃይል ሚዛን ፖለቲካ ፍላጎቶች ‘በበጎ የረጅ አዳኝነት ኃይል’ መጋረጃ ይሸሽጋል” ሲሉ ጽፈዋል ካፐል፡፡

ዋነኛው የትችታቸው ማረፊያ አፍሪካ ወደውጭ ለምትልካቸው የግብርና ምርቶች ተፎካካሪነት ደንቃራ ይሆናል ያሉት የአውሮፓ ኅብረት የግብርና ድጎማ ነው፡፡

“የአውሮፓ መንግስታት እና የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ርትዕ ባለው አኳኋን አይንቀሳቀሱም፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ለግብርናው ከፍተኛ ድጎማ እስካደረገ ድረስ፣ የአፍሪካ ገበሬዎች በአውሮፓ ገበያዎች ምንም ዓይነት ዕድል አይኖራቸውም፤ አውሮፓ ውስጥ የማይመረቱትን እንደቡና እና ካካዋ ያሉትን ከሚያቀርቡት በስተቀር” ሲሉ ይሟገታሉ ካፐል፡፡

18352138_303
ሮበርት ካፐል

ጀርመናዊው ምሁር የሚመለከታቸው የአገሪቱ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች የግብርና ድጎማ ጉዳይን በድጋሚ እንዲያጤኑ ብሎም አፍሪካ በምትልካቸው ምርቶች ላይ የተደነቀሩ የንግድ ጋሬጣዎችን የሚቀንስ የንግድ ፖሊሲን እንዲተገብሩ ምክረ-አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የአውሮፓ-አፍሪካ የንግድ ምክር ቤቶች የአፍሪካ ምርቶችን በአውሮፓ ኅብረት ይሸጡ ዘንድ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም በተጨማሪ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህም በጠቅላዩ ዕቅድ ላይ እንደታተተው አፍሪካ ውስጥ ላሉ የጀርመን ኩባንያዎች ‘የማማከር መረብ’ን ከመደገፍ ይልቅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

ካፐል እንደሚሉት “ይህ አጀንዳ ይበልጡኑ የራሷን ምርቶች እና ገበያ ተከላካይ እየሆነች የመጣችውን ዩኤስኤን (‘ቅድሚያ ለአሜሪካ’) በጽንሰ ኃሳብ አካክሶ በመመከት፣ እያደገ የሄደውን አፍሪካ በቻይና ላይ ያላትን ጥገኝነት እንዲቀንስ አስተዋጽዖ የሚያደርግ የትብብር ስትራቴጂ ይሆናል፡፡ ከአፍሪካ ጋር የሚደረገው የንግድ ግንኙነት ‘በከፍተኛ ደረጃ ወደፊት የሚገፉ’ ይሆናሉ ሲሉ ጥርት ባላለ ሁኔታ በደምሳሳው መናገር በቂ አይደለም፡፡ ምንም እንኳ ይህ መልካም ኃሳብ ቢመስልም፣ እዚህ ግባ የሚባል ፍሬ ነገር የለውም፡፡”

ዲሞክራሲያዊ እሴቶች እና የምጣኔ ኃብት ልማት

ጀርመን በአፍሪካ የተሰናሰለ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዳይኖራት ከሚፈታተኑ ተግዳሮቶች አንደኛው ምጣኔ ኃብታዊ ልማት እንዲሁም ዲሞክራሲያዊ ልማት እና ሰብዐዊ መብቶች ሁሌም እጅ ለእጅ ተያይዘው የማይገኙ መሆናቸው ነው፡፡ ጀርመን በኋለኛው ጉዳይ ላይ ያላትን ፖለቲካዊ አትኩሮት ‘በእሴት ላይ የተቃኘ’ ይሉታል፤ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አካል ቢሆንም ሁሌም ግን ወጥ አይደለም ባይ ናቸው፡፡

“የጠቅላዩ ዕቅድ ጸሐፊዎች ይህንን ጉዳይ አስበውበት ማንሳታቸው ተቀባይነት ያለው ነገር ነው፡፡ ይሁንና ማብራሪያዎቹ አሳማኝ አይደሉም፡፡ በእሴት ላይ የተቃኘ ፖሊሲ ግልጽ ሕግጋትን ይሻል፡፡ እነዚህ ግን በጠቅላዩ ዕቅድ ላይ ብዥ ባለ ሁኔታ በደምሳሳው ነው የተነሱት፡፡ በወጥነት በእሴት ላይ የተቃኘ ፖሊሲን መከተል በተራማጅ (ሪፎርም) እና በኢ-ተራማጅ (ነን-ሪፎርም) መንግስታት፣ በአምባገነን እና በዲሞክራሲያዊ አገራት መካከል ልዩነትን ለማስመር የሚያስችሉ መስፈርቶችን ማስቀመጥን ይጠይቃል” ሲል ይነበባል የኃሳብ አመንጭው ተቋም ሪፖርት፡፡

ካፐል አክለውም ጠቅላዩ ዕቅድ እደርስበታለሁ የሚለውን በእሴት የተቃኘ ፖሊሲ የሚቃረኑ የጀርመን የልማት የገንዘብ ድጋፍን ያሳያሉ ያሏቸውን ታሪካዊ ምሳሌዎች ያወሳሉ፡- “ለምሳሌ ያህል በአምባገነን የምትደዳረው ኢትዮጵያ ከፍ ያለ የገንዘብ ድጋፍ ለልማት ድጋፍ ተሰጥቷታል፤ እና ስለዚህም የጀርመን መንግስት ራሱ የበየነው የድጋፍ መስጫ መስፈርት ተጥሷል፡፡ ጠቅላዩ ዕቅድ ቶጎን፣ አልጀርያን፣ ግብጽን እና ቤኒንን ነው ሪፎርም መንግስታት ሲል የለየው፡፡ ይህም መሠረታዊ፣ በእሴት የተቃኘ ጽንሰ ኃሳብ በወጥነት እየተተገበረ እንዳልሆነ ያመላክታል፡፡”

“ከኢትዮጵያ እና ከሩዋንዳ ጋር የሚደረግ ከፍ ያለ ትብብር (ይህም መታቀዱ ግልጽ ነው)፣ ከጠቅላይ ዕቅዱ አዝማሚያ በተጻራሪ የሚቆምና በእሴት የተቃኘ ፖሊሲ ዙርያ ጥያቄን የሚያጭር ነው፡፡”

ጀርመን አምባገነን መንግስታትን ስትደግፍ እና ይህንንም ለምን እንደምታደርግ የበለጠ ሃቀኛ መሆን አለባት ይላሉ ካፐል፡፡ “ይህም ነባራዊውን እውነታ ያገናዘበ ፖለቲካ (ሪልፖለቲክ) እና ከአምባገነን መንግስታት ጋር የሚደረግ ትብብር ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ያደርገዋል…. ከእነዚህ አምባገነን መንግስታት ጋር ትብብር የሚደረግ ከሆነ፣ ጥርት ያሉ ደንቦች እና ሁኔታዎች ያስፈልጋሉ፡፡”

የጊጋን ሙሉ ሪፖርት እዚህ ማግኘት ይችላሉ፡፡