እ.ኤ.አ. በ፩፱፻ የፈረንሳይ የስነ ካርታ ባለሞያ ምጣኔ ሀብታዊ እና ስትራቴጅካዊ ዋጋ የላትም የተባለ በረሃማ የጠረፍ አካባቢ፣ ሰፊ አካባቢያዊ ፋይዳ ሊኖረው የሚችል ግጭት በኤርትራ እና ጅቡቲ መካከል ለመቀስቀሱ ምክንያት ሆናለች።

ጅቡቲ እንደምትለው እ.ኤ.አ. ሰኔ ፲፫ ቀን የኤርትራ የጦር ሐይሎች የጭቅጭቅ ማዕከል ወደሆኑት ስፍራዎች- የዱምዬራ ተራራዎች እና የዱምዬራ ደሴት- ተንቀሳቅሰዋል። በተመሳሳይ ዕለት የካታር የሰላም አስከባሪዎች በድንገት እና ያለማስጠንቀቂያ ለቅቀው ወጥተዋል። እ.ኤ.አ በ፶፻፲ በተደረሰው ስምምነት መሠረት የካታር ጦር ኃይል አባላት በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ ሰፍረው ነበር።

የካታር ጦር ኃይል አባላት ስፍራውን ለቅቀው የወጡት ጅቡቲ ከካታር ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን እና ካታር ለሽብርተኛነት እና ለመካከለኛው ምስራቅ ፅንፈኛ ቡድኖች ትሰጠዋለች የሚባለውን ድጋፍ እንድታቆም በሚደርስባት ጫና ከሳዑዲ አረቢያ መሩ ጥምረት ጋር መወገኗን ተከትሎ ነው።

ስለ ኤርትራ እና ጅቡቲ ውዝግብ የሚከተሉትን ጉዳዮች ማወቅ ይጠቅማል።

ታሪካዊ ስምምነቶች

እ.ኤ.አ. በ፶፻፲ በካታር አደራዳሪነት በኤርትራ እና በጅቡቲ መካከል በተደረገ ስምምነት መሠረት በካታር መሪ ሊቀ መንበርነት የሚንቀሳቀስ ኮሚቴ እንዲያቋቁሙ ተወስኖ የነበር ሲሆን፣ ይህ ስምምነት የድንበር ይገባኛል ውዝግቡን በመቅረፍ፣ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ እስኪደረስ ድረስ ካታር አወዛጋቢውን ክልል የማስተዳደር ኃላፊነት ይኖራታል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ግን ኮሚቴው ድንበር የማካለሉን ሥራ ሳያከናውን ቆይቷል።

ሌሎች ቀደም ያሉ ሁለት ስምምነቶች በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የሚያጠነጥኑ ሲሆን፣ አሁን ያለው ሁኔታ ህጋዊነታቸውን እና ፋይዳቸውን ጥያቄ ላይ የሚጥል ነው። አንደኛው እ.ኤ.አ የ፲፱፻ የፈረንሳይ-ጣልያን ስምምነት ሲሆን   ኬፕ ዱምዬራን ለሰሜናዊ ጣልያን (በኋላ ኤርትራ) ደቡባዊውን ክፍል ደግሞ ለፈረንሳይ (በኋላ ጅቡቲ) ይሰጣል።

በርዕሰ ምድሩ ጫፍ ላይ የምትገኘው የዱምዬራ ደሴት ጉዳይ በ፲፱፻ ስምምነት አልተቀረፈም። በመጀመሪያ ፈረንሳይም ሆነች ጣልያን በደረቁ አካባቢ ላይ ፍላጐት አልነበራቸውም። በ፲፱፻ በፈረንሳይ የሥነ ምድር ማኅበር የታተመው ዓመታዊ የሥነ ምድር መፅሐፍ የፈረንሳይ የኀሠሣ ቡድን ከጣልያኗ ቅኝ ግዛት ጋር የድንበር ማካለል ለመፈጸም መጓዙን ቢገልጽም የዱምዬራ ርዕሰ ምድር የረባ ዋጋ እንደሌለው ጨምሮ አስፍሮ አትቷል።

“ደረቅ እና ዐለታማው ምድር ከምጣኔ ኃብትና ስትራቴጅ አንፃር የረባ ጥቅም የሌለው ነው። ሰሜናዊው ክፍል ወደጣልያን ሲሄድ ደቡባዊ ክፍል ለፈረንሳይ ይሆናል” ሲል ይነበባል መፅሐፉ።

ይሁንና እ.ኤ.አ በ፲፱፴ዎቹ አጋማሽ  የተስፋፊነት ባህርይ የነበረው የጣልያን መንግስት የራስ ዱምዬራን ጠቅላላ ክልል እንዲሁም የቀይ ባሕርን ደሴት ይገቡኛል አለ። እ.ኤ.አ በ፲፱፻፴፯ በተደረሰ ስምምነት ፈረንሳይ ግዛቶቹን አሳልፋ ሰጠች። ነገር ግን ስምምነቱ በፈረንሳይ ብሔራዊ ምክር ቤት አልጸደቀም ነበር። ኤርትራ በስፍራው ላይ ያላትን የይገባኛል ጥያቄ ለመደገፍ የ፲፱፻፴፯ቱን ስምምነት ስታነሳ፣ ጅቡቲ በበኩሏ የጣልያን እና የፈረንሳይ ስምምነት ውድቅ ታደርገዋለች።

የ፳፻፰ቱ ፍልሚያ

እ.ኤ.አ. በወርሃ ሰኔ ፳፻፰ በኤርትራና በጅቡቲ አዋሳኝ ስፍራዎች በነበሩ ወታደሮች መካከል ጦርነት ተቀሰቀሰ። ነገር ግን ፍልሚያው ለጥቂት ቀናት ያህል ብቻ ነበር የቆየው። በሚያዝያ ፳፻፰ በራስ ዱሜዬራ ግዛቷ ላይ ወታደራዊ ሠፈራ እንደገነባች በመግላፅ ጅቡቲ አስመራን ወንጅላ ነበር። በምላሹም የራሷን ኃይሎች ወደአጨቃጫቂው ተራራማ የባህር ምድር ተዳፋትማ ስፍራዎች አስፍራለች።

ወታደራዊው ፍጥጫ ወደነውጥ መርቶ የኋላ ኋላ የተቀራረቡት ወታደሮች ተጋጭተዋል። በወቅቱ ቢቢሲ እንደዘገበው ግጭቱ የተቀሰቀሰው ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፰ በርካታ የኤርትራ ወታደሮች ጣብያቸውን በመልቀቅ ወደጅቡቲ ወገን መሸሻቸውን ተከትሎ ነው። ወዲያውኑም የጅቡቲ ኃይሎች የከዳተኞቹን መመለስ ከሚጠይቁ የኤርትራ ኃይሎች ጥቃት ደረሰባቸው። ይሁንና እነዚህ ዘገባዎች በጅቡቲ ምንጮች ላይ የተመሠረቱ ሲሆን ኤርትራም “ፀረ ኤርትራ” ናቸው ስትል ግጭቱ የተለኮሰው በከዳተኛ ወታደሮች ምክንያት መሆኑን ውድቅ አድርጋለች።

በግጭቱ በአስራዎች የሚቆጠሩ የጅቡቲ ወታደሮች ሲሞቱ ያንኑ ያህል ደግሞ ቆስለዋል። ሰኔ ፲፫ ቀን የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ጉሌህ አገራቸው ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ መሆኗን እንደተናገሩ የተጠቀሰ ሲሆን የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን ግጭቱን በማቃለል ጅቡቲ ኤርትራን ወደ “ንትርክ” ውስጥ ለማስገባት እየጣረች እንደሆነና ጉዳዩም “የተፈጠረ” መሆኑን ተናግረዋል። በውጭ አደራዳሪ መፍትሄ እንዲፈለግ ዓለም ዓቀፍ ጥሪ የቀረበ ሲሆን ግጭቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ረግቧል።

ዓለም አቀፍ አሰላለፍ በ፳፻፰ቱ ግጭት

በ፳፻፰ቱ የኤርትራና ጅቡቲ ግጭት ወቅት ከነበሩ የውጭ ተዋንያን መካከል ከሌሎች አገራት በተጨማሪ ፈረንሳይና ዩኤስ አሜሪካ ይገኙበታል። በግጭቱ ወቅት የፈረንሳይ ኃይሎች የግጭቱን አካባቢ ቅኝትን ጨምሮ ለጅቡቲ ጦር የሎጅስቲክስ፣ የደህንነት እና የህክምና ድጋፍ ማድረጋቸውን ይፋ አድርገዋል። በተጨማሪም ፈረንሳይ ጅቡቲ ውስጥ ያላትን ጣብያ እንደምታጠናክርም ገልፃለች።

የዩኤስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም የኤርትራን “ወታደራዊ ፀብ አጫሪነት” በማውገዝ ከጅቡቲ ጋር የወገነ ይመስላል። እንዲህ ያለው የውጭ ድጋፍ ምንም እንኳ የጅቡቲ ጦር በኤርትራ በአያሌው በቁጥር ቢበለጥም፣ ኤርትራ ከፈረንሳይ እና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ግጭት ውስጥ ሳትገባ የበለጠ ከባድ ጥቃት ጅቡቲ ላይ ልትሰነዝር አትችልም ማለት ነው።

ኤርትራ ውስጥ ያሉ የጅቡቲ እስረኞች

ጅቡቲን የሚቆጠቁጥ አንድ ጉዳይ ኤርትራ በ፳፻፰ቱ ግጭት ወቅት ማርካቸዋለች ተብላ የምትወነጀልባቸውን እስረኞች እስካሁንም ያለመልቀቋ ነው። ምንም እንኳ ካታር የተወሰኑ የጅቡቲ ምርኰኞችን በማስለቀቅ ስኬታማ ብትሆንም ሌሎች ግን የት እንዳሉ አይታወቅም።

እ.ኤ.አ በ፳፻፲፩ ሁለት ጅቡቲያዊያን ታሳሪዎች ከኤርትራ ያመለጡ ሲሆን ሌሎች አራት እስረኞች ደግሞ እ.ኤ.አ በ፳፻፲፮ በካታር አደራዳሪነት ተለቅቀው ወደጅቡቲ ተመልሰዋል። ይሁንና የተባበሩት መንግስታት በኤርትራ ላይ ያደረገው ምርመራ ሌሎች ፲፪ ተፋላሚዎች ኤርትራ ውስጥ የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ገልጿል። የኤርትራ መንግስት በበኩሉ አንድ ታሳሪ በይዞታው ስር እንዳለ ህይወቱ ማለፉን አምኗል።

“የኤርትራ መንግስት በይዞታው ስር ማንም ታሳሪ በህይወት እንደሌለ ለመርማሪው ቡድን አሳውቋል። ሁኔታው በትክክልም ይህ ከሆነ፣ ኤርትራ የሌሎቹ ተፋላሚዎች ህይወት ስላለፈበት አኳኋን፣ በፍልሚያ መኃል ይሁን በእስር ላይ ሳሉ መሆኑን ማረጋገጫ መስጠቷ እጅግ አስፈላጊ ነው… በእስር ላይ ሳሉ ከሆነ ደግሞ መቼ እንደሞቱና ስለተቀበሩበት ስፍራ” ሲል ይነበባል እ.ኤ.አ ጥቅምት ፳፻፲፮ የተፃፈ የተባበሩት መንግስት ሪፖርት። “ይህ የፀጥታው ምክር ቤት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ኤርትራ በምትገዛባቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በልማዳዊ ህግም የሚጠየቅ ነው።”

የኢትዮጵያ ሚና

በኤርትራና በጅቡቲ መካከል ያለው ውጥረት የነገሰበት ግንኙነት በከፊል የሚመነጨው እ.ኤ.አ ከ፲፱፻፺፰ እስከ ፳፻ ድረስ በተደረገው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጅቡቲ ኢትዮጵያን ደግፋ የነበር ከመሆኑ ነው። በዚያ ግጭት ወቅት ኢትዮጵያ የምፅዋ ወደብን የመጠቀም ዕድልን አጥታ ነበር። ጅቡቲ ቦታውን በመተካት ኢትዮጵያ ወደውጭ የምልካቸው ምርቶች ዋነኛ መተላለፊያ ሆነች። ምንም እንኳ ጅቡቲ ጦርነቱን ባትቀላቀልም ከኤርትራ ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋረጠች።

ርቃ በምትገኘው ባድመ አካባቢ ምክንያት የተቀሰቀሰው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያደረገችው ጦርነት አገሪቷ በድንበሯ አካባቢ አሉ ለምታስባቸው ጥቃቶች እና ሰርጐ ገብነቶች ስሱ እንድትሆን አድርጓታል። አስመራ እ.ኤ.አ በ፳፻፪ የተላለፈ የድንበር ውዝግብ ውሳኔ እንዳልተከበረ ነው የምታምነው። ውሳኔው ባድመን ለኤርትራ የሰጠ ሲሆን ነገር ግን እስካሁንም ድረስ ኢትዮጵያ ቦታውን እየተቆጣጠረች ትገኛለች። ይህም ኤርትራ ከጐረቤቶቿ ጋር ያሉባትን የድንበር ውዝግቦች አስመልክቶ የውጭ አደራዳሪዎችን እንዳታምን ምክንያት ሆኗል።

ካታር ያደራደረችው ስምምነት ደንቦች

በ፳፻፲ሩ የኤርትራ እና የጅቡቲ ስምምነት መሠረት ካታር አጨቃጫቂውን ሥፍራን የማሸማገል ኃላፊነት ሲኖራት በሁለቱ አገራት መካከል ቋሚ መፍትሄ ላይ የመድረሻ መንገድ ታፈላልጋለች። የጦር ምርኰኞችን እና የጠፉ ሰዎችን በማስመለስም ዋናውን ኃላፊነት ትወስዳለች። የስምምነቱ አንቀፅ ፮ እንዲህ ይላል፡- “በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ግጭት ለመቅረፍ በአደራዳሪነት ሚናዋ የካታር አገረ-መንግስት [የድንበር] ኮሚቴው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ እስኪደርስ ድረስ የድንበር ቁጥጥሩን ትመራለች…”

የካታር ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ቁጥር በግልፅ አልተቀመጠም። በቅርብ ይፋ የሆነ ሪፖርት የካታርን ጦር ፪፻ ይሆናል ብሎ የገመተ ቢሆንም ተመልካቾች ግን ከ፬፻ እስከ ፭፻ ከፍ እንደሚል ይገምታሉ።

ሁለት መቀመጫቸውን ካታር ያደረጉ ተመራማሪዎች ሱልጣን ባረካት እና ሳንሶም ሚልተን በአል ጄዚራ ድረ ገፅ ላይ ባሳተሙት ፅሁፍ በርቀት በሚገኙ አካባቢዎች በሰላም ማስከበር ሥራ መሰማራት “በሰፊው ምስጋና ቢስ ክንውን” መሆኑን ገልፀው ቋሚ የሰላም ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ሁለቱን አገራት በተለይም ኤርትራን ወቅሰዋል። ባራካትና ሚልተን የካታር ኃይሎች    ከአካባቢው ለቅቀው መውጣት በአሁኑ የገልፍ ቀውስ ጅቡቲ ወይንም ኤርትራ ከሳዑዲ ጋር ለመወገናቸው የተፈፀመ የበቀል እርምጃ ሳይሆን የ፳፲ሩን ስምምነት በመተግበር እርምጃ ሊታይ ባለመቻሉ ነው።

“የተኩስ አቁም ስምምነቱን ወደ ቋሚ የሰላም ስምምነት ለመቀየር ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም ትንሽ እርምጃ ብቻ ነው ሊመዘገብ የቻለው… ሁለቱ አገራት በተለይም ኤርትራ ለወሰን ማካለል የቀረበላቸውን ጥሪ ሊቀበሉ አልቻሉም። የድንበር ግጭቱን እንደኰስታራ ጉዳይ መያዝን ትተው እውነታውን ወደመካድ አምርተዋል። የካታር ሰላም አስከባሪዎች በስፍራው መኖር አገራቱን በጋራ በሚጠቀሙበት ግጭት አልባ ፍጥጫ እንዲመቻቹ አድርጓቸዋል።”

ይሁንና በካታሩ የዜና ድረ ገፅ ላይ የታተመው መጣጥፍ የጦር ኃይሉ መውጣት “ከኤርትራና ጅቡቲ ጋር በተፈጠረው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለውጥ ምክንያት መጠናከሩ ጥርጥር የለውም።”

መጣጥፉ ጨምሮም ካታር ከኤርትራ ጋርም ሆነ ኮጅቡቲ ጋር ካላት ግንኙነት በበለጠ ካለባት ውስጣዊ የደህንነት ፍላጐት ጋር የበለጠ የሚያገናኘው ነገር ሊኖር እንደሚችል ያብራራል። “፭፻ የጦር ኃይል ጠቅላላ ኃይሏ ፲፪፼ ብቻ ለሚሆን እና በታሪኳ እጅግ አጣዳፊውን ቀውስ እያስተናገደች ላለች አገር ብዙ ነው።”

የቅርብ ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ሁኔታዎችን ለማጤን የልዑካንን ቡድን ወደጅቡቲ ድንበር እንደሚልኩ አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሁኔታውን በዝግ የተወያየበት ሲሆን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሃቅ አፈላላጊ ቡድንን ወደጅቡቲ ድንበር ለማስፈር መወጠኑን ተቀብሎታል። የፀጥታው ምክር ቤት “ለመፃኢው ጊዜ የመተማመን ግንባታ እርምጃዎች እሳቤን” እንደሚቀበለው እና ሁኔታውን በቅርብ እንደሚከታተለው ገልጿል።

ኤርትራ በበኩሏ በመረጃ ሚኒስትሯ   በኩል በሰጠችው መግለጫ “በተናወጠ ከባቢ” የተከሰተውን “የተካለበ” የወታደሮቿን የማውጣት እርምጃ በተመለከተ ምንም ማብራሪያ እንዳልቀረበላት ገልፃለች።

Categories: Amharic News

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *